አርቆ ማየት፤ አልቆ ማሥራት

“አርቆ ማየት፤ አልቆ ማሥራት” በሚል መሪ ሐሳብ በደሴ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የደቡብ ወሎ ዞን አጠቃላይ አመራሮች የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲና የመንግሥት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በስኬት ተጠናቋል።

በመድረኩ ላይ የ2018 በጀት ዓመት የልማትና የፓርቲ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት የአሻጋሪ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ቀርበው ለሁለት ቀናት ያህል ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ይማም እንደገለጹት፣ ያለፈው በጀት ዓመት በብዙ ተፎካካሪ ሁኔታዎችና ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ በርካታ አዎንታዊ ውጤቶች የተመዘገቡበት፣ ለቀጣዩ የ25 ዓመታት የልማት ዕቅድ ጠንካራ መሠረት የተጣለበትና በክልላዊ ስኬቶች የፊት መስመር ላይ ለመሰለፍ ያስቻለ ውጤታማ የሥራ ዓመት ነበር።

በተቋማት ግንባታ፣ በልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በጸጥታና ሕግ ማስከበር ዘርፎች የተከናወኑ የተቀናጁ ጥረቶች ለአሁኑ ከፍተኛ አፈጻጸም ዋነኛ ምክንያት ሆነዋል ነው ያሉት አቶ አሊ።

የጋራ ግንዛቤን ከመፍጠርና አቅጣጫዎችን ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ከመተግበር አንጻር በየደረጃው ሰፊ ልዩነቶች በመኖራቸው፣ በወረዳዎች፣ በተቋማትና በአመራሩ መካከል የጐላ የአፈጻጸም መበላለጥ በመታየቱ ዓመቱ “ሳቢና ጎታች” ሁኔታዎች የታዩበትም ነበር ብለዋል።

በራዕይና ተልዕኮ ላይ ግልጽነት መፍጠር፣ የጠራ ዕቅድ ማዘጋጀት፣ ሕግ ማስከበርን አጠናክሮ መቀጠል፣ የመፈጸም አቅምን ማሳደግ፣ የውስጥ ገቢን ማሳደግ እና ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች ትኩረት መስጠት በቀጣይ ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ ዳኛው በበኩላቸው በዞኑ የተመዘገቡት የፖለቲካ፣ የሰላምና የልማት ድሎች በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራትና ለ25 ዓመታት ግቦች ትልቅ መነሻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፓርቲውን ቅቡልነት ማረጋገጥ፣ ልማትና መልካም አስተዳደርን ተቋማዊ ማድረግ፣ በሕዝባዊ ንቅናቄና በጸጥታ መዋቅር ቅንጅት ሰላምን ማስፈን እና 7ኛውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በስኬት ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሠርቷል ሲሉም አቶ ተስፋ አክለዋል።

በአመራሩና በመዋቅሩ የተቀናጀ እንቅስቃሴ የማህበረሰቡን አስተሳሰብ በመገንባት ጽንፈኝነትን በፖለቲካዊ የበላይነት ለመመከትና የሕዝቡን ድጋፍ ለማጠናከር ተችሏል።

ጸጋዎችን በአግባቡ ለይቶ አውቆና አቅዶ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተግባብቶ በማልማት በኩል ያሉ ውስንነቶች በአዲሱ በጀት ዓመት መስተካከል አለባቸው ሲሉም አቶ ተስፋ አስገንዝበዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን 2018 በጀት ዓመት በብዙ መለኪያዎች ውጤታማ አፈጻጸም የተመዘገበበትና የፓርቲ ቅቡልነት የተረጋገጠበት ዓመት መሆኑን አረጋግጠዋል።

ሕዝቡ የሰላም ባለቤት ሆኖ የፅንፈኛ ፍላጎት እንዲከሽፍ በማድረጉ አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍንና ለልማት የተመቸ አካባቢ እንዲፈጠር ተደርጓል፤ ችግርን መቋቋም የሚችል አመራር በመፍጠር በኩልም መሻሻል ታይቷል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው።

ዋና አስተዳደራው ከሕዝቡ ፍላጎት አንጻር አመራሩ ከፍ ባለ ሁኔታ አስቦ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበው፣ የአካባቢን ጸጋዎች ለይቶ በማቀድና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተግባብቶ ተግባሩን በክትትልና ግምገማ የመምራት ውስንነቶች ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በ2019 በጀት ዓመት መዋቅራዊ ሽግግርን ለማምጣትና የሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ግብርናን ጨምሮ በልዩ ርብርብ መሠራት እንዳለበት ዋና አስተዳደሪው አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ .ር)በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ የመንግሥት ግንዛቤና ሥነ-ልቦናው ከፍ ያለ አመራርና መዋቅር መፈጠር በመጀመሩ ስኬታማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።

የተፈጠረውን የጸጥታ ቀውስ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚጠቀም አመራር በመፈጠሩ ደቡብ ወሎን ጨምሮ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ስኬታማ አፈጻጸሞች ተመዝግበዋል፤ ለኢኮኖሚ መመንጠቅ መሠረት የሚጥል የሀብት ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አፈጻጸሞች ላይ የታዩ ጎደሎዎችን ማረም እንደሚያስፈልግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

በአጠቃላይ መልካም ልምዶችን መሠረት በማድረግ በአዲሱ በጀት ዓመት “አቅዶና አልቆ መፈጸም” እንደሚገባ አሳስበው፣ ግብርናን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል

23 views 0 likes
Share Telegram WhatsApp